ቀጥታ፡

በግብርና እና ሌሎችም የኢንቨሰትመንት መስኮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ ይደረጋል 

ሰቆጣ ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡-  በግብርና እና ሌሎችም የኢንቨሰትመንት መስኮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ የሚደረግ መሆኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ተናገሩ። 

በሰቆጣ ከተማ በአንድ ባለሀብት 25 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ዛሬ ተመርቆ ተከፍቷል።

ማዕከሉ በህገ ወጥ ይቀርብ የነበረውን የዘር፣ የጸረ አረምና ሌሎች ግብአቶች በማስቀረት አርሶ አደሩ የሚልገውን ግብአት በወቅቱ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል።



በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንታይቱ ካሴ ባደረጉት ንግግር፤ የማዕከሉ መገንባት ግብአትን በወቅቱ በማድረስ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም አርሶ አደሩ የግብአት እጥረት ያጋጥመኛል ከሚል ስጋት ወጥቶ በግብርና ስራው ላይ እንዲያተኩር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የተጀመረው ተግባር መልካም መሆኑን አፈ ጉባዔዋ ጠቁመው፤ በግብርና እና ሌሎችም የኢንቨስትመንት መስኮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚደረግ ተናግረዋል።



"ማዕከሉ ጥራቱን የጠበቀ የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሮች ተደራሽ የሚያደርግ ነው" ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ናቸው

በህገ ወጥ ይቀርብ የነበረውን የዘር፣ የጸረ አረምና ሌሎች ግብአቶች በማስቀረት አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ግብአት በወቅቱ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።



የግብርና ግብአት በዓይነትና በሚፊለገው መጠን በማቅረብ ምርታማነት አድጎ በአስተዳደሩ የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለማቃለል አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አቶ አዲስ አብራርተዋል።

የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አዳነ ባህሩ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማዕከሉ አርሶ አደሩን የሰብልና የእንስሳት ልማት በዘመናዊ መልኩ እንዲያካሂድ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርምር ማዕከሉ የሚወጡ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በስፋት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የማዕከሉ መገንባት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የማዕከሉ ባለቤት አቶ ሲሳይ አወጣ ፤ ማዕከሉ የሰብል፣ የቋሚ ተክል ዘር፣ ፣ የፀረ አረምና ተባይ ኬሚካል፣ የእንስሳት መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን በቀጥታ ለአርሶ አደሩ የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ 25 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ለስድስት የዘርፉ ባለሙያዎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ማዕከሉ እንዲቋቋም የስልጠናና ሌላም ድጋፍ ማድረጉ ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም