የወንዝ ዳርቻ፣ የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወንዝ ዳርቻ፣ የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- የወንዝ ዳርቻ፣ የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ የሙያ ማህበር ከሳንባ በሽታና ሌሎች ፅኑ ህመሞች ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ የመተንፈሻ ህመሞች ዙሪያ የሚሰራ ማህበራዊ ተቋም ነው።
ማህበሩ የአየር ንብረት ለውጥ በመተንፈሻ አካላት ላይ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ እንዴት መቀነስ ይቻላል በሚል 11ኛውን ዓመታዊ ኮንፍረንስ አካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ፤ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ራሄል አርጋው እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ መንግስት ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ሰፋፊ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስምምነት በመፈጸም በሀገሪቱ ያለውን የአካባቢ ብክለት ለመቀነስ እና ንጹህ ከባቢ ሁኔታ እንዲኖር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመሩት የወንዝ ዳርቻ ፣ የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሮች የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል፡፡
የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚቻል አረጋግጠዋል፡፡
የሶሳይቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ራሄል አርጋው፤ የአየር ንብረት ለውጥ በመተንፈሻ አካላት በተለይም በሳምባ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ መድረኩ ተጽዕኖውን ለማስረዳት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮንፍረንሱ በቲቢ፣ አስም፣ ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካል፣ ካንሰርና ተያያዥ የጤና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ህብረተሰቡ በሽታውን በትራንስፖርት፣ በቢሮና በቤት ውስጥ መስኮት በመክፈት መከላከል እንደሚገባው አስታውቀዋል፡፡
የበሽታው ምልክት የሆኑት ሳል፣ የድካም ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሲከሰት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮንፍረንሱ ህብረተሰቡ በመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና በበሽታው ላይ የሚደረግ ምርምርን ለመደገፍ ያለመ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡