ቀጥታ፡

የማህበረሰቡ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ መተላለፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን

አሶሳ፤ የካቲት 13/2017(ኢዜአ):- የማህበረሰቡ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ መተላለፍ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለጸ።

ሰባተኛው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባህል እና "ዋዛ" ፌስቲቫል በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።

ባለስልጣኑ "ዋዛ" የተሰኘውን ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያን በዓለም ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ያካሄደው ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ የማይዳሰሱ ቅርሶች እና የማህበረሰቡ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንድተላለፉ ለማድረግ እየሰራ ነው።


 

እስከአሁን ድረስ ስድስት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

በዚህ ዓመት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነውን "ዋዛ" ባህላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያን ለማስመዝገብ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የዚህ መድረክ ዓላማም የማህበረሰቡ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ምክክር እንዲያደርጉበት ነው ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብድሳ በበኩላቸው "ዋዛ"ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ለሚደረገው ጥረት የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።


 

"ዋዛ" ን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ከፌዴራል ተቋማት ጋር እያደረገ ያለው ዝግጅት የሚደነቅ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ እና የቤኒሻንጉል ብሔረሰብ ምክር ቤት ጋር ላለፉት ሶስት ዓመታት ማህበረሰቡን ያሳተፈ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ምስክያ አብደላ ናቸው።

የሙዚቃ መሣሪያው ዕውቅና ቢያገኝ ሙያተኞች መሳሪያውን ከዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር አዋህደው እንዲጠቀሙ ያግዛል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብና ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የማህበረሰቡ ተወካዮች እና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም