የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ ነው - ቫለንቲና ማትቬዬንኮ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ ነው - ቫለንቲና ማትቬዬንኮ
አዲስ አበባ፤የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በጠንካራ እና በማይናጋ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀመንበር ቫለንቲና ማትቬዬንኮ ገለጹ።
ቫለንቲና ማትቬዬንኮ ፥ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ያካሄዱትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ቀትር ላይ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለምክር ቤቱ ሊቀመንበር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማሪፊያ በመገኘት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡
ሊቀመንበሯ ቫለንቲና ማትቬዬንኮ በኢትዮጵያ በተደረገላቸው ድንቅ አቀባበል በራሴ እና በልዑካኑ ቡድን ስም ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት በእጅጉ መደሰታቸውን እና የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጠንካራና የማይናጋ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፥ የልዑካን ቡድኑ ባለፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ በመገኘት ያካሄደው የሥራ ጉብኝት እና ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ተናግረዋል።
በሩሲያ እና ኢትዮጵያ መካከል ለረዥም ዘመናት ጸንቶ የቆየው መልካም ዲፕሎማሲያዊ አጋርነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።