ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ተስማሙ
አዲስ አበባ ፤የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በሀገራቱ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን ለማሳደግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በሩሲያ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ማክሲም ራሽቲኒኮቭ ከተመራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ኮሚሽነር ዘለቀ፥ መንግስት የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ እና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተገበራቸው ያሉ ሪፎርሞች እና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት እያደረጋቸው የሚገኙ ጥረቶችን አስመልክቶ ለልዑኩ ገለጻ አድርገዋል።
ኮሚሽነሩ የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ሁለንተናዊ ግንኙነት በኢኮኖሚያዊና የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ዘርፍ እንዲያድግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የሩስያ ኢኮኖሚ ሚኒስትር ማክሲም ራሽቲኒኮቭ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ እና በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ያላትን ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት አላት ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በማዕድን ሀብት ልማት፣ በአፈር ማዳበሪያ ምርት፣ በታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እና ማሰራጨት፣ የመረጃና ቴክኖሎጂ ዘርፎችና የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማዘመንን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሀገራቱ በጋራ ሊያለሟቸው የሚችሏቸውን የኢንቨስትመንት ዘርፎችና ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመለየት የሚያስችል የኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ ፎረሞችን በቀጣይነት በጋራ እንደሚያካሂዱ መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።