አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሀገራትን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት በማሳለጥ ዜጎች ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያገኙ ያስችላል

አዲስ አበባ፤የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና የሀገራትን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት በማሳለጥ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያገኙ እንደሚያስችል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ባለሙያ አንዱአለም ጎሹ (ዶ/ር) ገለጹ።

አንዱአለም ጎሹ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የአህጉሪቷን ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ስራ ላይ ለማዋል ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራት እየሰሩበት መሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

የነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ የአፍሪካን የታሪፍ ስርዓት በማስተካከል የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።

አፍሪካ ዕምቅ የመልማት ጸጋ አላት ያሉት ባለሙያው፥ ለዚህም ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ማሳለጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ይህም የአፍሪካን ኢንዱስትሪ ሽግግር ማሳለጥ የሚያስችል የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምኅዳር ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የንግድ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የአህጉሪቷን ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያገኙ በማስቻል የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስም አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በአመዛኙ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው ተግባር ላይ ሲውል ከውጪ ለሚገቡ ምርቶች የሚከፈልን ከፍተኛ ቀረጥ በመቀነስ ሀገራት የሚገበያዩበትን ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ወደ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ የሚገቡ አባል ሀገራትም የንግድና ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን በማሳለጥ ለአህጉሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም ለነፃ ንግድ ቀጣናው ስምምነት ትግበራ ተወዳዳሪነትን የሚያሳልጡ ዘርፎችን በመለየት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ማስቀጠል እንደሚጠበቅባት ጠቁመዋል።

በተለይም በኃይል አቅርቦት፣በግብርና የኢንዱስትሪ ሽግግር፣በማዕድን፣ ቴክኖሎጂ እና በአገልግሎት ዘርፍ ሂደቱን በጥንቃቄ በመምራት ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም