የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረም በጁባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረም በጁባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፡-ሁለተኛው የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረም ከግንቦት 17 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም በጁባ ይደረጋል።
ፎረሙን ለማካሄድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ስራዎች መጀመራቸውን በጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ኮሚቴው ኤምባሲውን ጨምሮ የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር፣የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣የደቡብ ሱዳን ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር፣የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ግብርና ምክር ቤት እና በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ቢዝነስ ኮሚዩኒቲን ያካተተ ነው።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ፎረም እ.አ.አ ግንቦት ወር 2024 በጁባ መካሄዱ የሚታወስ ነው።
ፎረሙ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንትን ትብብር ማጠናከር ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
በተጨማሪም የአገራቱን የንግድ ማህበረሰቦች ግንኙነት የማጎልበት አላማንም አንግቧል።