ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤የካቲት 13/2017(ኢዜአ)፦ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የክትባቱን አስፈላጊነትና መርሃ ግብር በሚመለከት በኢንስቲትዩቱ የፖሊዮ ወረርሺኝ ምላሽ አስተባባሪ አቶ ሚኪያስ አላዩ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፥ ዘመቻው ለአራት ቀናት የሚቆይ ነው ብለዋል።
የፖሊዮ በሽታ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እንደሚከሰት ጠቅሰው፥ ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት ላይ የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የፖሊዮ ስርጭትን ለመካከል ክትባቱን በመደበኛና በዘመቻ መልክ ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያነሱት።
በአዲስ አበባ ከተማ፣በአማራ፣ አፋርና ጋምቤላ ክልሎች ላይ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር ድረስ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ መካሄዱንም አስታውሰዋል።
ከነገ ጀምሮ በፖሊዮ ክትባት ዘመቻው በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በዘጠኝ ክልሎች ሀገር አቀፍ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ይካሄዳል ብለዋል።
በዘመቻው እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 14 ሚሊየን ለሚጠጉ ህፃናት ክትባቱን ለመስጠት መታቀዱን አብራርተዋል።
ክትባቱ ቤት ለቤት በሚሰጥ አገልግሎት፣በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በህፃናት ማቆያና በጤና ተቋማት በነፃ እንደሚሰጠጥም ጠቁመዋል።
ለዚህም ከ84 ሺህ በላይ ባለሙያዎች ክትባቱን መስጠት የሚያስችል ዝግጅት አድርገዋል ነው ያሉት።
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለፖሊዮ ከሚሰጠው ክትባት በተጨማሪ መደበኛ ክትባቶችን ተከታትለው ላልተከተቡ የሚሰጥ በመሆኑ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
ለዚህም ህጻናት ክትባቱን በሚፈለገው መልኩ እንዲያገኙ፣ወላጆች፣ አሳዳጊዎችና ማህበረሰቡ ህጻናቱን በአግባቡ እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል።