በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ አስደናቂ ነው - የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ አስደናቂ ነው - የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ አስደናቂ ነው ሲሉ የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር ገለጹ።
የኢትዮጵያና የእንግሊዝ የኢኮኖሚ የትብብር ዘርፎች ላይ ያተኮረ መግለጫ በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች ተሰጥቷል።
የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ አስደናቂ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ልማት ትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ የእንግሊዝ ባለሀብቶች በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስትመንታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ በይፋ የጀመረችውን የካፒታል ገበያ በይበልጥ ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጀመረችውን ጉዞ ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ በዘርፉ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ መንግስት የወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ኢኮኖሚውን እንዳነቃቁት ገልጸዋል።
በዚህም በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ትላልቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች የበለጠ ትርፋማ በመሆን በኢኮኖሚው ላይ የተሻለ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፈጣን የዕድገት ጉዞ ላይ ናት ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የእንግሊዝ መንግስት በተለያዩ የልማት ስራዎች እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ እንደገለጹት፤ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ጨምሮ ቁልፍ ተቋማት እንዲቋቋሙ አድርጓል።
በዚህም የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የእንግሊዝ መንግስት ገበያው ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ላደረገው የቴክኒክ እና መሰል ድጋፎች ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም ግንኙነቱን ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ጋር እንደሚሰራ አመላክተዋል።