ቀጥታ፡

የሩሲያው የዜና እና የሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ስፑትኒክ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፈተ

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፦የሩሲያው የዜና እና ሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈቱን ይፋ አደረገ።

በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን ፌዴራል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ፣ የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ዲፕሎማቶች እና ጥሪ የተረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባው "ስፑትኒክ አፍሪካ" የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥት ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብር የኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን የያዘ አደረጃጀት እንዳለውም ተገልጿል።

ስፑትኒክ አፍሪካ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ድምጽ በመሆን እድገትና ብልጽግናቸውን ለማሳካት አጋዥ ሚና እንደሚወጣም ተጠቁሟል።

የሩሲያ ፌዴሬሽን ፌዴራል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ እንዳሉት፣ስፑትኒክ አፍሪካ የአፍሪካውያን ጥቅምና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው።

የስፑትኒክ አፍሪካን ቢሮ መከፈት ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር የማጠናከር ግብ ለማሳካት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሩሲያና ኢትዮጵያ በባህል፣ በእምነትና በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዳላቸው ገልጸው፥ ስፑትኒክ አፍሪካ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ትክክለኛ መረጃ በማውጣት አንዱ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ነው ያሉት።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፥ ስፑትኒክ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ተደራሽ በመሆኑ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ ለዓለም በማስተዋወቅ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

የስፑትኒክ አፍሪካ በአዲስ አበባ መከፈቱ የሁለቱን ሀገራት ትብብር የሚያሳይና የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበራዊና ሁሉን አቀፍ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ተጨማሪ የትብብር መንገድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሚዲያው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም