ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ተደንቄያለሁ-የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ተደንቄያለሁ-የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር እያስመዘገበችው ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳስደነቃቸው የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ ገለጹ።
አዲስ አበባም አስደማሚ ለውጥ ላይ መሆኗን ማየታቸውን ተናግረዋል።
በአፈ ጉባኤዋ የተመራ የልዑክ ቡድን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ጋር ውይይት አድርጓል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ፥ የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ታሪካዊና ልዩ ነው ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት የትብብር ግንኙነት በመሪዎች ደረጃም ከፍ ያለ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በሩሲያ ያደረጉትን ጉብኝት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና ልዑካን ቡድናቸው በኢትዮጵያ እያደረጉት የሚገኘው ጉብኝትም የሀገራቱን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ መሸጋገርን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሩሲያ በጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዱ ውሳኔዎች እንዳይተላለፉ ያሳየችውን የድጋፍ አቋም እናደንቃለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ የኢንቨስትመንት የትብብር መስኮች ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ታላቅና ታሪካዊ ሀገር ናት ብለዋል።
የገናና ታሪክ፣ የባህላዊ እሴቶች እና የውብ መስህብ ስፍራዎች ባለቤት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ ሲመጡ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ገልጸው፥ለዚህም አመስግነዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋርም ትላንት በብዙ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ጠቅሰዋል።
አክለውም፥በጠቅላይት ሚኒስትር ዐቢይ፥ በሳል የአመራር ሰጪነት ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ፥ የአዲስ አበባ ለውጥ እንዳስደመማቸውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተች ስለመምጣቷም አንስተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረት አባል በመሆን የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ በባለብዙ ወገንና በሁለትዮሽ የትብብር መድረኮች ላይ እየሰራች መሆኗን ጠቅሰዋል።
ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው ጉብኝትም የሁለቱን ሀገራት ትብብር በተለያዩ መስኮች ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።