ቀጥታ፡

በአፋር ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት አበረታች ናቸው

ሰመራ፤የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት አበረታችና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አባላት ገለጹ።

የጋራ ምክር ቤቱ አመራር አባላት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፥ ከውይይታቸው በተጓዳኝ በአፋር ክልል እየተሰሩ የሚገኙትን የልማት ተግባራትን ተመልክተዋል።

በአባላቱ ከተጎበኙ የልማት ሥራዎች መካከል የጨው ፋብሪካ፣ የመኖ ማቀነባበሪያ፣ ሎጊያ የሚገኘው የከብቶች ማድለቢያ እና የመስኖ ስንዴ ልማት ይገኙባቸዋል።

በጉብኝት ስነ ስርዓቱ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የምክር ቤቱ አመራር አባላት በጉብኝታቸው እንደገለጹት፥ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚ እድገት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፥በአፋር ክልል ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወኑ ካሉ የልማት ተግባራት ውስጥ የእንሰሳት መኖ ዝግጅትና አጠቃቀም ተመልክተናል ብለዋል።

በዚህም 300 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ካለው በተጨማሪም ለማስፋፋት ጥረቱ መልካም መሆኑን ጠቁመው፥ የልማት ስራ የእንሰሳትን ምርታማነት ለመጨመር የሚያግዝ እንደሆነ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ የእንሰሳት መኖ ፍጆታን ለመሸፈን አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው የጋራ ምክር ቤቱ አባል መብራቱ ዓለሙ(ዶ/ር)፥ የአፋር ክልል ከሚታወቅባቸው አንዱ የሆነውን የጨው ምርትን በተመለከተ በፋብሪካ ደረጃ ያለውን የአመራረት ሂደት ለመመልከት ችለናል ብለዋል።

ክልሉ ለአገር ኢኮኖሚ የሚተርፍ ሰፊ ሀብት እንዳለው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አመራር አባል አቶ ዮሃንስ መኮንን በበኩላቸው፥በክልሉ የተመለከቷቸው የልማት ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፥ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም