ቀጥታ፡

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም፣ መቻቻል እና አብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና አላቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡- የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም፣ መቻቻል እና አብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና እንዳላቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገልጿል።

ባለፉት ሶስት አመታት 43 የሚሆኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ሰውነት ማግኘታቸውን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ፣ በማሳወቅ፣ በማስተማርና በማዝናናት እንዲሁም የዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግስታዊ መብት ተግባራዊ እንዲደረግ ያግዛሉ።

የተለያዩ አመለካከቶችንና አስተያየቶችን በማስተናገድ ዲሞክራሲ ስርዓት እንዲዳብር እና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው።

በተለይም የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም፣ መቻቻል እና አብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና አላቸው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ባለፉት ሶስት አመታት 43 የሚሆኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ሰውነት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም 8 የሚሆኑ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ሰውነት የሚያገኙበት መንገድ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ህጋዊ ሰውነት ማግኘታቸው ለሚያከናውኑት ማንኛውም ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙሃን ካላቸው ሰፊ ተደራሽነት አንፃር በአግባቡ መቃኘት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የጋራ በሆኑ ጥቅሞች ላይ ተቀራርበው መስራት እና እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በጋራ መፍታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህም ተቋማቱ በጋራ የሚሰሩበት አውድ መፈጠሩንም አመላክተዋል።

ሃይማኖቶች የየራሳቸው አስተምህሮ ቢኖራቸውም ትልቅ ቦታ የሚወስደው የሰላም ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጋራ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል ሰላም አንዱ በመሆኑና ይህንኑ በስራዎቻቸው ማንጸባረቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን የሚወጡ ይዘቶች በርካቶች የሚጋሯቸው በመሆኑ የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን ታሳቢ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም