ቀጥታ፡

በክልሉ ከመኸር እርሻ ከ44 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ወልቂጤ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከመኸር እርሻ ከ44 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።

በበጋ ወቅት መደበኛ የመስኖ ልማት ሥራም በክልሉ ከ146 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱም ተመላክቷል።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) የክልሉን የአስፈፃሚ ተቋማት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ለክልሉ ምክር ቤት አቅርበዋል።

በሪፖርቱም በክልሉ የመኸር እርሻ ወቅት ከ557 ሺህ 230 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን ገልጽዋል።

በዚህም ከ44 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።


 

የክልሉን የግብርና አቅም አሟጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካትና ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉለህ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በቅንጅት መሰራቱን ተናግረዋል።

ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብአትና ለቴክኖሎጂ አቅርቦትና አጠቃቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ድጋፍና ክትትል ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በተሰራው ሥራ የተገኘው ውጤት ገበያን ለማረጋጋት እያገዘ ነው ብለዋል።

በክልሉ ግብርናን ለማሳደግ የተጀመረው ቅንጅታዊ ጥረት በአዳዲስ እሳቤዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አሁን ላይ በበጋ ወቅት በሚከናወን መደበኛ መስኖ ልማት ከ146 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱንም አንስተዋል።


 

ክልሉ ያለውን የገቢ አማራጭ አሟጦ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመፍታት በተደረገ እንቅስቃሴም ከ6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመው፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 39 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

በግማሽ በጀት ዓመቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ በተከናወኑ ሥራዎች ከ215 ሺህ በላይ ዜጎችን በጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ነው ያሉት።

በትምህርት ዘርፍ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል የሚያችል የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ሥራን ጨምሮ የግብአትና የመምህራን አቅም ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍም በሽታን መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ በተለይ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በግማሽ በጀት ዓመቱ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች በክልሉ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄና አስተያየት በማቅረብ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም