የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ፓርላሜንታዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መጥቷል - አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ፓርላሜንታዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መጥቷል - አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ፓርላሜንታዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መምጣቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ ፌዴሬሽን ፌደራል ምክር ቤት አፈጉባዔ ቫለንቲና ማትቬዬንኮ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ የሰጡት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፥ በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን አንስተዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በአፈ ጉባኤ ቫለንቲና ከተመራው ልዑክ ጋር ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በኃይል ዘርፍ፣ በኢንፎርሜሽን ደህንነት እና የመገናኛ ቴክኖሎጂ መስክ ያለውን ትብብር ማጠናከር ላይም ትኩረት ያደረገ ውይይት መደረጉን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና በሩሲያ የተጀመረው ፓርላሜንታዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መግባባት ላይ መደረሱን አፈጉባኤ አገኘሁ ገልጸዋል።