የንግድ ትርኢትና ባዛሩ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመትና የሥራ ዕድል ለማግኘት አስችሎናል - የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ትርኢትና ባዛሩ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመትና የሥራ ዕድል ለማግኘት አስችሎናል - የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች

ሚዛን አማን፤ የካቲት 12/2017(ኢዜአ)፡-በሚዛን አማን ከተማ የተከፈተው ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመትና የሥራ ዕድል ለማግኘት እንዳስቻላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የሚዛን አማን ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ካዘጋጁት ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር የሚገኘው ገቢም ለከተማዋ የኮሪደር ልማት እንደሚውል ታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች የንግድ ትርኢትና በዛሩ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱና የሥራ እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
አቶ ምስጋናው ገብረ ሚካኤል የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ እንዳሉት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ነጋዴዎች በባዛሩ መሳተፋቸው የፈለጉትን ምርት በቅርበት ለመሸመት አስችሏቸዋል።
በባዛሩ የተለያዩ የፋብሪካ ውጤቶች በመቅረባቸው የሚፈልጓቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸመቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የከተማዋ የንግድ ሥራ እንዲነቃቃ ባዛሩ የራሱ አስተዋጾ እንዳለው ጠቅሰው ከንግድ፣ ትርኢትና ባዛሩ የሚገኘው ገቢ ለከተመዋ የኮሪደር ልማት የሚውል በመሆኑ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።
በባዛሩ የሚፈልጓቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አዜብ ከድር የተባሉ የከማዋ ነዋሪ ናቸው።
ባዛሩ የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ፋይዳ ስላለው በቀጣይም መጠናከር እንዳለበት የገለጹት ነዋሪዋ ለቀጣይ የንግድ ትስስር በመፍጠር ገበያን ለማረጋጋት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
“በባዛሩ የሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶችን በመጫንና በማውረድ ሥራ ዕድል ተፈጥሮልናል” ያለው ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪው ወጣት እስራኤል ሀብታሙ ነው።
"ቃይጻ አትስኗት" በተሰኘ ማኅበር ውስጥ ተደራጅቶ እየሰራ ያለው ወጣት መለሰ ታል በበኩሉ፣ በባዛሩ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን በፈረቃ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግሯል።
የሚዛን አማን ከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አምሳለ ነጋሽ በበኩላቸው፣ በባዛሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ከ100 በላይ ነጋዴዎች ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ባዛሩ በገበያው የምርቶችን ዋጋ ማረጋጋትና ለሸማቾች የተሟላ ምርት ማቅረብን ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ ባዘሩ እስከ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ከባዛሩ የሚገኘው ገቢ በከተማው እየተካሄደ ላለው የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚውል በመገንዘብ ምርቶችን በመግዛት ለከተማው ዕድገት አስተዋጾ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።