የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረው ሥራ ውጤታማ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረው ሥራ ውጤታማ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያውያን የጋራ ፕሮጀክትን ስኬታማ ለማድረግ የጀመራቸው ስራዎች ውጤታማ ናቸው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሶስት ዓመት የስራ አፈፃፀም በማድመጥ የሥራ ዘመኑንም ለአንድ ዓመት አራዝሟል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ከጥርጣሬ እና ሥጋት በመላቀቅ ሀገርን ለማጽናት ምክክሩ መልካም አጋጣሚ ነው።
ለሀገርና ለትውልድ ቀጣይነት በቅንነትና በስክነት ተናጋግረን ለመውጪ ትውልድ ጥሩ ነገር ማስተላለፍ እንደሚገባ ያመለከቱት አፈ ጉባዔው፤ ኮሚሽኑ የጀመራቸው ተግባራት እጅግ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቀጣይ ጉዟችንን ለማሳካት ኮሚሽኑ የጀመረውን አስደናቂ ሥራ ማገዝ ይገባናል ሲሉም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም የምክክር አጀንዳዎችን አስመልክቶ በተከናወኑ ተግባራት በ10 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የምክክር፤ የአጀንዳ ልየታ እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎች ተጠናቋል ብለዋል።
በሀገራዊ ኮንፍረንስ ላይ የሚሳተፉ 1 ሺህ 105 የወረዳ ማህበረሰብን በመወከል የሚሳተፉ ተወካዮች መለየታቸውንና አጀንዳ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በዚህም በድምጽ፣ በምስል እና በጽሁፍ የተለያዩ መረጃዎች መሰብሰብ መቻሉንና በዲጂታል መንገድ እንዲሰነዱ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ 1ሺህ 234 ወረዳዎችን በመለየት አካታችና አሳታፊ የሆነ ምክክር ለማካሄድ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራ እንዲሳካ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ትጥቅ የፈቱ በሀገራዊ የምክክር መድረክ መሳተፋቸውንም ጠቁመዋል።
በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መስራት ይኖርብናል ሲሉም የመንግስት ተጠሪው ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመን ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።
ምክር ቤቱም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ታላላቅ ሀገራዊ ስራዎች እንዲያጠናቅቅ የሥራ ዘመኑን ለአንድ ዓመት አራዝሟል።
የምክር ቤቱ አባላትም የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወነው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ የኮሚሽኑ የስራ ጊዜ ለአንድ አመት መረዛሙ ቀሪውን ስራ እንዲያጠናቀቅ ያግዘዋል ብለዋል።