ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የኢትዮ-ቬትናም የጋራ የፖለቲካ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፡- የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የሶሻሊስት ሪፐብሊክ ቬትናም የጋራ የፖለቲካ ምክክር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በፖለቲካ ምክክሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል የፈጠረ በመሆኑ የቬትናም ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሩ አቅርበዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ከቬትናም ፈጣን የኢንዱስትሪ እድገት ልምዶችን ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላትም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የቬትናም ልዑካን ቡድን መሪ የሶሻሊስት ሪፐብሊክ ቬትናም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ኑየን ሚን ሄን በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለውን ፈጣን የማኀበረ-ኢኮኖሚ ዕድገት በቅርብ እንደሚከታተሉ መናገራቸውም ተጠቅሷል።


 

ምክትል ሚኒስትሯ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውም እንዲሁ።

ሁለቱ ሀገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በባለብዙ ወገን መድረክ እና በደቡብ ደቡብ ትብብር ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በፖለቲካ ምክክሩ ወቅት ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ቬትናም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በቀጣይ ዓመት እንደሚያከብሩም ተገልጿል።

ሁለተኛውን የፖለቲካ ምክክር በቀጣይ ዓመት ለማካሄድ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም