ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራው እንዲሳካ መንግስት ቁርጠኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራው እንዲሳካ መንግስት ቁርጠኛ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራው እንዲሳካ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የተከማቹ ቅሬታዎችንና ችግሮችን ይፈታል ተብሎ የታመነበትና በብዙ የሀገሪቱ ዜጎች ቅቡልነት ያገኘ እና ተስፋ የተጣለበት ተቋም መሆኑን አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ በገለልተኛነት ለሚያከናውናቸው ተግባራት መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ቁርጠኝነቱን እያሳየ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለአብነትም በቅርቡ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ትጥቅ የፈቱ ታጣቂ ሀይሎች በሀገራዊ የምክክር መድረክ መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከጠመንጃ ውጪ በጠረጴዛ ዙሪያ እነጋገራለሁ ለሚል ማንኛውም አካል መንግስት በሩን ክፍት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ለስኬቱም ሁሉም አካል ከሚያራራርቁ ሀሳቦች ይልቅ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች አተኩሮ መስራት እንዳለበት መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የስራ ዘመኑ የሚጠናቀቀውን የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመን ለአንድ አመት እንዲራዘም ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳቡን አቅርቧል።
ምክር ቤቱም በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመራቸውን ታላላቅ ሀገራዊ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ የስራ ዘመኑን በሶስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ለአንድ ዓመት አራዝሟል።