በምስራቅ ቦረና ዞን በአዲስ መልክ የተደራጁ 104 የቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ነው። - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በአዲስ መልክ የተደራጁ 104 የቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ነው።
ነገሌ ቦረና ፤ የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ቦረና ዞን በአዲስ መልክ የተደራጁ 104 የቀበሌ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በነገሌ ቦረና ከተማ በ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የህዝብ ተሳትፎ የተገነባ ባህላዊ ፍርድ ቤትና የቀበሌ አስተዳደር አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የምስራቅ ቦረና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ያሲን መሀመድ፤ በዞኑ 104 ቀበሌዎች በአዲስ መልክ መደራጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
አደረጃጀቶቹ ቀደም ሲል ከወረዳ ወደ ዞን በተደጋጋሚ የሚመጡ ቅሬታዎችን በመፍታት የጊዜና የሀብት ብክነትን እየፈቱ ነው ብለዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ለማድረግ በሁሉም ቀበሌዎች ከ700 በላይ አመራሮችና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች መመደባቸውን ጠቁመዋል፡፡
የቀበሌ አደረጃጀቶቹን ለማጠናከር በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች በህዝብ ተሳትፎ የቀበሌ ጽህፈት ቤት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በነጌሌ ቦረና ከተማም በህዝብ ተሳትፎ የተገነቡ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችና የቀበሌ መስተዳደር ጽህፈት ቤቶችም የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከነጌሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መብራቱ ባህሩና ወይዘሮ ታየች ወርቅነህ፤ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ለማገኘት ከወረዳ እስከ ዞን ድረስ በሚደረግ ምልልስ ገንዘብና ጊዜ ሲባክን ነበር ብለዋል፡፡
አዲሱ አደረጃጀት የጊዜ፤ ቀጠሮና የስራ መንዛዛትን በማስቀረት ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት እንደረዳቸው ተናግረዋል።
ለባህል ፍርድ ቤቱ ግንባታ በሚችሉት አቅም ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው በቀጣይም ለጋራ ልማት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።