ቀጥታ፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ ተማሪዎችን በማካካሻ ትምህርት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 11 /2017(ኢዜአ)፡- በደብረማርቆስ ከተማ ትምህርት ቤቶች በማጠናከሪያና በማካካሻ ክፍለ ጊዜ በማመቻቸት ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊው አቶ ያምራል ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአካባቢው የነበረው ችግር በመማር ማስተማሩ ተግባር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል።

ችግሩ እየተቃለለ አሁን ላይ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የአመራር አባላትና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ እንቅስቃሴ በርካቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ወደ ትምህርት ገበታቸው ለተመለሱ ተማሪዎች የማጠናከሪያና የማካካሽ የትምህርት ክፍለ ጊዜ በማመቻቸት ለማብቃት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ባለድርሻ አካላት ማገዝ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱ ተማሪዎችን ቅዳሜና አሁድን ጨምሮ ባላቸው የትርፍ ሰዓት የማስተማሩን ስራ በማጠናከር የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ እቅድ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የአምበሽ የመጀመሪያደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አበራ ዲንቃ በበኩላቸው፤ ህጻናትን በትምህርታቸው ለማብቃት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከተማሪ ወላጆች መካከል የወንቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሸጋው ጌጡ፤ ከመንግስት ጎን በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ልጆቻቸው ተረጋግተው በመማር ውጤታማ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።



በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ27ሺህ በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ከአስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም