ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣ ነው - የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጌዜ ጀምሮ ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባዔ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ 3 ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጌዜ ጀምሮ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ እንዲሁም ባህላዊ የግጭት አፈታት፣ የሽምግል እና በርካታ ሀገር በቀል እሴቶች ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ይሁንና ላለፉት 60 ዓመታት ያክል ያልተፈቱና በአሁኑ ጊዜ ስር የሰደዱ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡት ችግሮቻችን ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት እንዳንገነባ፣ አሰባሳቢ ትርክት እንዳይኖረን በዚህም ድሃ እና ተመጽዋች እንድንሆን አድርገውናል ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ከችግሮቿ ለመውጣት የተለያዩ እድሎች ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም፤ በተለይ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በተለያዩ ምሁራን በተፈጠረ አለመግባባት እድሎችን መጠቀም ሳይቻል መቅረቱንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለእነዚህ የተወዘፉ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የተቋቋመ መሆኑንና ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ማብራራታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኮሚሽኑ የምክክሩ ሂደት አሳታፊ እና አካታች እንዲሆን ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች እንደሆነም የመንግስት ዋና ተጠሪው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሀገራዊ መግባባት እንዳይፈጠር ያደረጉት ሀሳቦች በሙሉ መካተታቸውን ማረጋገጥና ሁሉም የተለያዩ ሀሳቦች እንዲወከሉ ማድረግ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም