ቀጥታ፡

ቱሪዝም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ሁሉን አቀፍ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው -ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፤የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፦ቱሪዝም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበርክት ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ “ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልለኔ ስዩም ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሚኒስትሯ በፕሮግራሙ ላይ መንግስት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት እና ዘላቂ ልማት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ሀገሪቷ ያላት ብዝሃነት እና የምድረ ቀደምትነት ታሪክ በጣም የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ይሁንና በመስኩ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ዘላቂ ተጠቃሚነት የመቀየር ተግባር በሚፈለገው ደረጃ ሳይሰራበት መቆየቱን አመልክተዋል።

ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ነባር የቱሪዝም ስፍራዎች የማልማት፣ አዳዲስ የቱሪዝም ስፍራዎች የመገንባት፣ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር የመጨመር፣ የአሰራር ማዕቀፎች ዝግጅት እና የቱሪዝም ስፍራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ የማስተዋወቅ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩ “የገበታ ለሸገር” እና “የገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት ረገድ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

በመዲናዋ የሚገኙት የወዳጅነት አደባባይ፣ አንድነት ፓርክ፣ ሳይንስ ሙዚየም እና አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው የአዲስ አበባ መልክ በአዲስ ሁኔታ በመግለጥ የጎብኚዎች ዓይን ይበልጥ እንዲያርፍባት ማድረጉን ገልጸዋል።

እድሳት የተደረገላቸው ብሔራዊ ቤተ መንግስት፣ የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስታት እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ለቱሪዝም ዘርፉ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ነው የገለጹት።

በሁነቶች ወይም የማይስ ቱሪዝም ለስብሰባዎች፣ጉባዔዎች እና ለተለያዩ ሁነቶች የሚመጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች የቆይታ ጊዜ በማራዘም የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ከአገር ውስጥ ባለፈ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ የቱሪዝም ትብብሮች የማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከአገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ እና ባለሀብቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋንያን በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ነው ያብራሩት።

በአጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እና ዘላቂ ልማት ውስጥ ቀጣይነት ያለው አበርክቶ እንዲኖረው የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም