የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት የገለጠ፤የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ያሳየ ነው -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት የገለጠ፤የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ያሳየ ነው -የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፦38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ የገለጠ፤ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና 46ኛው የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ፍፃሜን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ እንግዶች የተሳተፉበት እንከን የለሽ መስተንግዶ እንደነበር ገልጸዋል።
በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና አረብኛ ቋንቋዎች የሰለጠኑ የበጎ ፈቃደኛ ካዴቶችን በማሰማራት ስኬታማ የዲፕሎማሲና የልዩ መስተንግዶ ስራዎች ተከናወነዋል ብለዋል።
የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽን፣ የመብራት፣ ኢንተርኔት እና ሌሎች አገልግሎቶች የተሳለጡና የእንግዶችን ምቾት የጠበቁ እንደነበሩ ገልጸዋል።
በሕብረቱ ጉባኤ 57 ልዩ ፕሬዝዳንታዊ ቻርተር በረራዎችን በብቃት ማስተናገድ መቻሉን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ አቀባበል ልዩ እንደነበር ከተሳታፊዎች መገለፁን ተናግረው፤ ምስጋና አቅርበዋል።
አዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ ውብ ሌሎች ሀገራት ልምድ ሊወስዱባት የሚገባ መሆኗን ከተማዋን ተዘዋውረው የጎበኙ መሪዎች መግለጻቸውን ተናግረዋል።
የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት ሁነት እንደነበርም አንስተዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ደምቀው እንዲወጡ ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆን እንደምትችል አቅጣጫ የጠቆመ ሁነት እንደነበርም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ላበረከተችው አስተዋፅኦ እውቅና የሚሰጥ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ የገለጠ፤ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ያስተላለፉት መልዕክት እና ከመሪዎች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች፣ የቀዳማዊት እመቤቶች መድረክ እና ሌሎችም ሁነቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠበቁ እንደነበሩ አንስተዋል።