በከተማዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤የካቲት 11/2017(ኢዜአ)፦የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ የ2ኛ ዙር ተጠቃሚዎች ምረቃ መርሐ ግብር በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።
መርሃግብሩ ከተለያዩ ስልጠናዎች ባሻገር ወጣቶች በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ለስድስት ወራት የተግባር ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ለስራ የሚያስፈልጋቸውን ክህሎትና ልምድ እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው።
በዛሬው ዕለትም በሁለተኛ ዙር ከ48 ወረዳዎች የተወጣጡ የ13 ሺህ 527 ወጣቶች ተመርቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ በከተማዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ142 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማት መርሐ ግብሩም ከ70ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፤ ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ የወጣቶችን ሰርቶ የመለወጥ ዕድል እያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው "ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ" አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 የሀገሪቱ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ከ15 ሺህ 731 በላይ ወጣቶች ስልጠና ማግኘታቸውን ጠቁመው ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በሁለተኛው ዙር ከ24 ሺህ 213 ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ከ21 ሺህ በላይ የሚሆኑት የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውንና ሶሰተኛ ዙር እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች የህይወታቸው የመጀመሪያው ምዕራፍ መስፈንጠሪያ ሊያደረጉት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም በበኩላቸው፥ የዓለም ባንክ የወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ መሣተፉን ይቀጥላል ብለዋል።
ተመራቂ ወጣቶቹ የሀገሪቱ ዕድገት ከማፋጠን አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጥራቱ በየነ፥ ቢሮው የስራ አጥ ምጣኔን ለመቀነስ በማሰብ ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድን ተግባራዊ በማድረግ በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮግራሙ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ወጣቶቹ ለስድስት ወራት የስራ ላይ ልምምድ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
በሁለተኛው ዙር ከ13 ሺህ በላይ ወጣቶች የልምምድ ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ 99 በመቶ የሚሆኑት በአለማማጅ ድርጅቶች ውስጥ የስራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱም ዙሮች ከ20 ሺህ በላይ የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፥ አሁን ላይ በርካታ ወጣቶች የሙያም የስራም ባለቤት መሆን መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።