የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ግብረ ሃይሉ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ግብረ ሃይሉ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ክልልን ሠላም ለማስጠበቅ ግብረ ሃይሉ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ የጋራ ግብረ ሃይል የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን ገምግሟል።
የጋራ ግብረ ሃይሉ በክልሉ ጸጥታ ጉዳይ ላይ የተወያየ ሲሆን በክልሉ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችንና ከደቡብ ሱዳን አጎራባች ወረዳዎች የሚሰነዘሩ የሙርሌ ጎሳዎች ጥቃት እና ዝርፊዎችን እንዲሁም የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ተወያይቷል።
የጋራ ግብረ ሃይሉ ከሪፖርቱ ጎን ለጎንም በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በመድረኩ እንዳሉት የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ግብረ ሃይሉ ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።
በክልሉ የወርቅ ቁፋሮን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ አካባቢዎች ህገ-ወጥ የደን ምንጣሮ መኖሩ እንደተደረሰበት ገልጸው የግጭት ምንጭ እንዳይሆን በቁርጠኝነት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
ወንጀል ሰርተው የሚደበቁ አካላትን አስመልክቶም ህብረተሰቡ አሳልፎ በመስጠት ረገድ አስደናቂ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የክልሉን ፖሊስ አስመልክቶ እንዳሉት ህገመንግስቱን በማያከብሩና ፖሊሳዊ ስነምግባር የሌላቸውን ግብረ ሃይሉ እንደማይታገስ ተናግረዋል።
ድንበር አካባቢ የሚገኙ ወረዳዎችን ፀጥታ ለማስጠበቅ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በኢታንግ ልዩ ወረዳ አካባቢ ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶን በዘላቂነት ለማስወገድ የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ውይይቶች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ሰላማችንን በማስጠበቅ ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር ሠላም የሠፈነባትና የበለፀገች ጋምቤላን እውን ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ግብረ ሃይሉ ገልጿል።
የዳሉል ማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ሜጀር ጀነራል አብድሮ ከድር በመድረኩ እንዳሉት የጋራ ግብረ ሃይሉ በክልሉ ግጭቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
አክለውም የክልሉን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ አመራሩ እራሱን በማጥራት በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትልዋክ ሮን(ዶ/ር) በበኩላቸው የጋራ ግብረ ሃይሉ ችግሮችን ከምንጩ ለማስወገድ አስቀድሞ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ፈጣንና ቀልጣፋ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ የክልሉን ሠላም በፅኑ መሠረት ላይ ልንገነባ ይገባል ብለዋል።