ተመድ እና የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የጋራ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ተመድ እና የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የጋራ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ
አዲስ አበባ፤የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፦የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝመሪ ዲ ካርሎ እና ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር(ዶ/ር) ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ፥ ከረዳት ዋና ፀሐፊዋ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ እና ቀጣናዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ሚኒስትር ጌዲዮን (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክር ሒደት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብም በቅርብ እየተከታተለው እና እየደገፈው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከቀጣናዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘም ኢትዮጵያ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ሁሌም ድጋፍ እንደምትሰጥ አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸው በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን በመግለጽ ቀጣናዊ ችግሮች መፍታት የሚቻለው በውይይት ብቻ ነው ብለዋል።
የተመድ. የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ በበኩላቸው ድርጅቱ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥም ሆነ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለምታደርገው ጥረት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በተያያዘም ጌዲዮን (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር (ዶ/ር) ጋር በአፍሪካ ቀንድ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸው በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሱዳንን በተመለከተም ኢትዮጵያ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ለሚደረግ ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ልዩ መልዕክተኛዋ ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣናው እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መሥራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።