በሀረር ከተማ የተገነቡት የኦሮሞ ባህላዊ ቤቶች ባህሉንና ታሪኩን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያስችላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረር ከተማ የተገነቡት የኦሮሞ ባህላዊ ቤቶች ባህሉንና ታሪኩን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያስችላሉ

ሐረር፤ የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፦ በሀረር ከተማ የተገነቡት የኦሮሞ ባህላዊ ቤቶች የኦሮሞ ህዝብ ባህል፤ታሪክና ማንነትን ይበልጥ ለማሳደግና ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ መሆናቸውን አባ ገዳዎች ገልፀዋል።
ባህላዊ ቤቶቹ የኦሮሞ ህዝብ ማንነትና እሴትን በሚያንፀባርቅ መልኩ የተገነቡ እና ባህሉን ጠብቆ በማቆየት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ሀረር አንድ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ መሆኗን የገለፁት አባገዳዎቹ ባህላዊ ቤቶቹ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን አክለዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ከሀረሪ ህዝብ ጋር የሚጋራቸው በርካታ እሴቶች እንዳሉት በመጠቆም ባህላዊ ቤቶቹ በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል ቀድሞ የነበሩ የአብሮነትና የወንድማማችነት መንፈስ ይበልጥ እንዲዳብር ተጨማሪ አቅም የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባህላዊ ቤቶቹ በተለይ በሀረሪ እና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር የሚያሴሩ አካላትን ሴራ ያከሸፈ እና ሀረር የሁላችንም የጋራ ቤት መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ባህል፤ታሪክና ማንነት ይበልጥ ለማጎልበት የተከናወኑ ተግባራት ደስታን እንደፈጠረባቸው የገለፁት አባገዳዎቹ የክልሉ መንግስት ላከናወናቸው አበረታች ተግባራት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የክልሉ መንግስት በከተማ እና ገጠር ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር እያከናወናቸው የሚገኙ የኮሪደር ልማቶች የቀድሞ ምልከታን የቀየሩ ናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።