የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፍሪካ የሚያጋጥማትን የሰላምና ደኅንነት ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ወሳኝ ትምህርት የሰጠ ነው - የአፍሪካ ሕብረት - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፍሪካ የሚያጋጥማትን የሰላምና ደኅንነት ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ወሳኝ ትምህርት የሰጠ ነው - የአፍሪካ ሕብረት
አዲስ አበባ፤የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፍሪካ የሚያጋጥማትን የሰላምና ደኅንነት ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ወሳኝ ትምህርት የሰጠ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ።
በአፍሪካ ሕብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሂደት የተገኙ ስኬቶችን አስመልክቶ የአፈፃጸም ሪፖርት ውይይት ተካሂዷል።
በዚህ ውይይት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፣ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ፣ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የፌዴራል መንግስት፣ የአፍሪካ ሕብረትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች ተገኝተዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዱዬ፥ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተካሄደው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሂደት የተገኙ ስኬቶችን ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም የአፍሪካ ሕብረት የመሪነት ሚና፣ የባለቤትነት ተነሳሽነት፣ የተደራዳሪ ምርጫ፣ የመገናኛ ብዙኅን አስተዳደር፣ የአሳታፊነት ዕይታ፣ የስምምነቱ የፋይናንስ ሂደት፣ የመደራደሪያ ቦታ መረጣ፣ ወሳኝ ሰዎችን የማካተት ሂደት፣ የተግባር ውክልና፣ የተፈፃሚነት ወሰን እና የሰላም ስምምነት ፍፃሜ አስራ አንዱ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሂደት ምርጥ ተሞክሮ መሆናቸው አንስተዋል።
በዚህም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ሀገራትን እየፈተነ የሚገኘውን የሰላምና ጸጥታ ችግር በአፍሪካዊ መፍትሔ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ወሳኝ ትምህርት የሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ፥ የደቡብ አፍሪካውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈፃጸም ሂደትና ቀጣይ ተግባራት ገለፃ አድርገዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፥ የሰሜኑን ግጭት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲቋጭ መደረጉ የኢትዮጵያን መንግስት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያሳየና የአፍሪካን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው።
በትግራይ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የመልሶ ግንባታ ስራዎችም የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ውጤት ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት ያለውን ቁርጠኝነት ለማጠናከር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የትግራይ ህዝብ ሰላም እንዲያገኝ በማድረግ የአፍሪካን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።