ቀጥታ፡

38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2017(ኢዜአ)፡- 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገር የሚጠበቅባትን አከናውናለች። አቀባበሉ፣ መስተንግዶውና መርሐ ግብሮቹ እንግዶቻችንን ያስደመመ ነበር ብለዋል።

እንግዶቿ የማይረሳ ትውስታ፣ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች። በዚህ የተነሣ የቆይታ ጊዜያቸውን ያራዘሙ እንግዶች ብዙ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዓላማዎች እና መርሖች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት በጉባኤው ዝግጅትና መስተንግዶ በተግባር አሳይታለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዘጋጅ ኮሚቴው፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የፕሮቶኮል ባለሞያዎች፣ የቴሌና የመብራት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብና የሰርከስ አባላት፣ ሆቴሎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፣ የጽዳት ባለሞያዎች፣ እንደ አንድ ልብ ሰሚ፣ እንደ አንድ አካል ፈጻሚ ሆነው ተሠርተዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ለእንግዶቹ ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት፣ መንገዶች ሲዘጉ በትዕግሥት በመጠባበቅ፣ ለጉባኤው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል።

ለሁላችሁም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉም አመስግነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት።

ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት በሥርዓት እና በዲሲፕሊን በመሥራታችን እንግዶቻችንን አስደምመናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገራችንን ከፍታ አሳይተናል ነው ያሉት።

ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑት የሚዲያ ሰዎች መልካም ገጽታችንን ለዓለም አሳይተዋል። ከዐሥር ሺ ዎች የሚልቁት እንግዶች እየበለጸገች ስለምትገኘው ሀገራችን ምስክሮች ሆነዋል ብለዋል።

ይህ ትብብራችንና ለሀገራችን ስኬት ያለን ቁርጠኝነት፣ ከጉባኤው በኋላም እንደሚቀጥል አምናለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆንዋ በዐለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል ነው ያሉት።

በድጋሜ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም