የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአንድነት ባስመዘገቡት ለውጥና የልማት ስኬት ተደንቄያለሁ - የኢስዋቲኒ ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአንድነት ባስመዘገቡት ለውጥና የልማት ስኬት ተደንቄያለሁ - የኢስዋቲኒ ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአንድነት ባስመዘገቡት ለውጥና የልማት ስኬት በእጅጉ መደነቃቸውን የኢስዋቲኒ ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ እና የኢስዋቲኒ ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ውይይትና ጉብኝት አድርገዋል።
እ.አ.አ ከ1986 ጀምሮ በ18 አመታቸው የኢስዋቲኒ ንጉሥ የሆኑት ምስዋቲ ሣልሳዊ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፥ በፕሬዝዳንቱ ግብዣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ቤተመንግሥቱ በርካታ ታሪኮችን በውስጡ የያዘ መሆኑንም ተመልክቻለሁ ብለዋል።
ቀደምት አፍሪካውያን መሪዎች ለአፍሪካ አንድነት የመከሩበት የጋራ ማዕድ የቆረሱበት፣ በጥቅሉ የአፍሪካን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ትልልቅ ውሳኔዎችን ያሳለፉበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህም ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ የኢትዮጵያ መሪዎች ለአፍሪካ ያደረጉትን ጉልህ አስተዋፅኦ የሚዘክር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸው አስደማሚ ለውጦችን መመልከታቸውንም ነው ንጉሡ የገለጹት።
በተለይም መንግሥትና ህዝብ በአንድነት ባደረጉት ጥረት በመሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም የልማት መስኮች አስደናቂ ለውጦች መመልከታቸውን ገልጸው፥ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡም የታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ህዝብ ለመላው አፍሪካውያን ባደረጉት ደማቅ አቀባበልና ልዩ መስተንግዶ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በህብረቱ ጉባኤም የተሻለች አፍሪካን መገንባት የሚያስችሉ ጠንካራ አጀንዳዎች ላይ ምክክር መደረጉን ነው ንጉሥ ምስዋቲ ሣልሳዊ የጠቀሱት።
የአፍሪካ መሪዎች የአህጉሪቱን ሽግግር ለማፋጠን ቁርጠኝነታቸውን ዳግም ማረጋገጣቸውን በማንሳት፥ አሁንም ለታላላቅ ስኬቶች በአንድነት መነሳት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኤስዋቲኒ ከፈረንጆቹ 2004 ጀምሮ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ዲፕሎማሲያዊ ትብብራቸውን እያሳለጡ ይገኛሉ።