ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ አዲስ ተመራጮች የአፍሪካን አጀንዳዎች ውጤታማ እንደሚያደርጉ ጽኑ እምነት አላት

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲስ ተመራጭ አመራሮች የአህጉሪቷን የጋራ አጀንዳ እውን ያደርጋሉ ብላ በጽኑ እንደምታምን ገለጸች።

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ"የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤው በዛሬው ውሎው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች ምርጫን አካሄዷል።

በምርጫው የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማህሙድ አሊ የሱፍ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እንዲሁም በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ቋሚ መልዕክተኛ ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አዲስ ለተመረጡት የህብረቱ ኮሚሽን አመራሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ በአዲሱ ተመራጮች አመራርነት የአፍሪካ አጀንዳ ይበልጥ ፍሬያማ እንደሚሆን ሙሉ እምነት እንዳላት ገልጿል።

አመራሮቹ ያላቸው የካበተ ልምድ የአህጉሪቷ ሰፊ ውጥኖች እንዲሳኩ የራሱን ሚና እንደሚጫወት በመግለጫው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ተመራጮቹ በቆይታቸው ጊዜ ለሚያከናውኑት ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም