ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ፦ - ኢዜአ አማርኛ
ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ፦

ቻዳዊው ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ሙሳ ፋቂ ማህማት እ.አ.አ ሰኔ 21 ቀን 1960 በምስራቃዊ ቻድ በምትገኘው ቢልታይን ከተማ ተወለዱ፤
እ.አ.አ በ1986 በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮንጎ ሪፐብሊክ ብራዛቪል በሚገኘው ማሪየን ኑጉዋቢ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፤
ከእ.አ.አ ከ1996 እስከ 1999 የቻድ ብሔራዊ የስኳር ኩባንያ (ሶናሱት) ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፤
እ.አ.አ ከ1999 እስከ 2002 የቻድ ፕሬዚዳት የካቢኔ ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ እ.አ.አ በ2001 በቻድ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የእድሪስ ዴቢ የምርጫ ቅስቀሳ ሃላፊ ነበሩ፤
እ.አ.አ በወቅቱ የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ሃሩን ካባዲ ተመርጠው በ2001 የቻድ የትራንስፖርት ሚኒስትር በመሆን ለአንድ ዓመት ሰርተዋል፤
የቀድሞው የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቤ ሙሳ ፋቂ ማህማትን በሃሩን ካባዲ ቦታ በመተካት እ.አ.አ በ2003 የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል፤
እ.አ.አ በ2008 በወቅቱ የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሱፍ ሳሌህ አባስ የሚመራው መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሆናቸውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ እ.አ.አ እስከ 2017 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል፤
ሙሳ ፋቂ ማህማት እ.አ.አ በ2017 በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ምርጫ በመወዳደር ተፎካካሪያቸው የነበሩትን ኬንያዊቷን ዲፕሎማት አሚና ሞሐመድን በማሸነፍ የሕብረቱ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ፤
የቻዱ ዲፕሎማት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ በአፍሪካ ሰላምና ልማት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
ሙሳ ፋቂ ማህማት እ.አ.አ በ2021 ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት በተደረገው ምርጫ ብቻቸውን ለእጩነት ቀርበው በድጋሚ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው በመመረጥ ለአራት ዓመት አገልግለዋል።
ከፓሪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙት የ61 ዓመቱ ዲፕሎማት ሙሳ ፋቂ ማህማት የቻድ ገዢ ፓርቲ ‘ፓትሪዮቲክ ሳልቬሽን ሙቭመንት’ አባል ሲሆኑ፤ ከ30 ዓመት በላይ በዲፕሎማሲና ፖለቲካ ዘርፍ አገልግሎት አላቸው።
ሙሳ ፋቂ የስምንት ዓመት የስራ ዘመናቸውን ዛሬ አጠናቀዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ በጀመረው የ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ ዛሬ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
ሚኒስትሩ የቻዱን ዲፕሎማት ቦታ በይፋ ተረክበው ለቀጣይ አራት ዓመታት ያገለግላሉ።
ሙሳ ፋቂ ማህማት የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛና እንግሊዘኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ።