ቀጥታ፡

ግሎባል ፈንድ ኢትዮጵያ በመድሃኒት ክምችትና ስርጭትን ለማዘመን የጀመረችውን ጥረት አደነቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2017 (ኢዜአ)፡- ግሎባል ፈንድ ኢትዮጵያ የመድሃኒት ክምችትና ስርጭትን በቴክኖሎጂ በማዘመን እመርታዊ ለውጥ አምጥታለች ሲል አደነቀ።

የግሎባል ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትን የመድሃኒት ማከማቻ ስፍራዎችና የስርጭት ሂደትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

ፒተር ሳንድስ እንዳሉት ኢትዮጵያ እና ግሎባል ፈንድ በጤናው ዘርፍ በትብብር መስራት ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጤና ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትብብራቸው እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።

ግሎባል ፈንድ በዘርፉ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ድጋፉን ለታለመለት ዓላማ በማዋል ከፍተኛ ውጤት ማምጣቷንም አረጋግጠዋል።

በተለይ ደግሞ የመድሃኒት ክምችትና ስርጭትን በቴክኖሎጂ በማዘመን እመርታዊ ለውጥ ማምጣቷን ነው የገለጹት።

ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የጤና ስርዓት መጠናከር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው፤ ግሎባል ፈንድ ባደረገው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ የመድሃኒት አገልግሎትን የሚያዘምን ዲጅታል ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ቀልጣፋ የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ስርዓት መገንባቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም