በአፍሪካ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ

 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የስርዓተ ምግብ ሽግግርን ለማሳካት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት(ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ ገለፁ።

"ከፖሊሲ ወደ ተግባር፥ በአፍሪካ የተመጣጠነ የሥነ-ምግብ እጥረትን ለመፍታት የጋራ አቋም መያዝ" በሚል መሪ ሃሳብ የአፍሪካ ሕብረት የጤና፣ ሰብዓዊ ጉዳዮችና ማህበራዊ ልማት የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 

በመድረኩም የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአህጉሪቱ መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የቀድሞው የኬኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተገኝተዋል። 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፥ ዓለማችን በምግብ ዋስትና ችግርና በተመጣጠነ ምግብ ሥርዓት አለመመጣጠን እየተፈተነች ነው ብለዋል። 

በተለይም በአፍሪካ የሚስተዋለው የምግብ ዋስትና እና የስርዓተ ምግብ ችግር በአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት ግንባታ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የግብርና ምርታማነትን በማረጋገጥ የተሻሻለ የምግብ ስርዓትን መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመው፥ ለዚህም የፋኦ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

በመድረኩ የተገኙት የሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳም ማቲካኔ፥ በአፍሪካ የተመጣጠነ የምግብ ስርዓት መጓደል የሰው ሃብትና የኢኮኖሚ ልማት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል። 

በመሆኑም የትውልዱን የምግብ ደህንነት ማረጋገጥና የተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን መገንባት ለነገ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በግብርና፣ በትምህርት እና በጤና አጠባበቅ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ማሻሻል እንዲሁም የህፃናት አመጋገብ፣ የእናቶች ጤና እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ ፖሊሲ መተግበር ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ቀጣናዊ የልማት፣ የትብብር እና የንግድ አቅርቦት ውጤታማነት ምክትል ፕሬዚዳንት ኒና ንዋቡፎ በበኩላቸው፥ በአፍሪካ የተሻለ ስርዓተ ምግብ ለመፍጠር የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 

ኢትዮጵያ ታዳጊዎች የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበት ዘላቂ ስርዓት ለመገንባት በሁሉም መስክ እያደረገች የምትገኘው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቀጣይም የአህጉሪቱን የምግብ አቅርቦትና ሥርዓት ለማጠናከር የአፍሪካ ልማት ባንክ  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም