ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው
አሶሳ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- በዘንድሮው ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽህፈት ቤቱ በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥቷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ለሜሳ ኔኖ እንደገለፁት በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የህዳሴ ግድብ ዳር ለማድረስ ከክልሉ ባለሀብቶች እና ነጋዴዎች 50 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዟል።
ግድቡ የኢትዮጵያውያን ኩራት እና የሁሉም አሻራ ያረፈበት መሆኑን ገልጸው የክልሉ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የታቀደውን ድጋፍ በማሰባሰብ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የክልሉ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አከለ ላዕከማርያም ከክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ጋር በመተባበር የንግዱ ማህበረሰብ ቦንድ እንዲገዛና ግድቡን እንዲጎበኝ ይደረጋል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ቦንዱን በስጦታ፣ በወለድና በወለድ አልባ መግዛት እንደሚችል ገልፀዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ በሀገራዊ ፕሮጀክት እንዲሳተፍ የንቅናቄ ስራ እንሰራለን ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አህመድ ከሊፋ ናቸው።