ህገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

ደብር ብርሃን፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦በደብረ ብርሃን ከተማ ህገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን በማጠናከር ለቁጥጥርና ክትትል ተግባሩ ስኬታማነት የበኩሉን እንዲወጣ የከተማ አስተዳደሩ ጠየቀ።

የከተማ አስተዳደሩ በህገወጥ የነዳጅ ዝውውርና ስርጭትን ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃሐማሁ ኮስትሬ በውይይቱ ላይ ነዳጅን በአግባቡ ማሰራጨትና መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመንግስት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚገባውን ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ከማዳያዎች በማውጣት የሚያከማቹና የሚቸረችሩ ግለሰቦች እጥረት ከመፍጠር ባለፈ በዚህ ምክንያት በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እየደረ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትና ሰርጭትን መከላከል የከተማ አስተዳደሩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡ ህገወጦችን እንዲያጋልጥ ጠይቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ንግድ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ይርጋለም ምስጋናው በበኩላቸው የህገወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚሰራባቸው ዘርፎች የነዳጅ ጉዳይ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

አንዳንድ ነዳጅ ማደያዎች ህገወጥነትን ከመታገል ይልቅ ችግሩ እንዲባባስ እያደረጉ እንዳለ ጠቅሰው ባለፉት 7 ወራት 7 ሺህ 293 ሊትር ናፍጣና ቤንዚል በህገወጥነት ሲቀሳቀስ መያዙን ተናግረዋል።

በከተማው የሚገኘው 'የኒወን' ነዳጅ ማደያ ስራ አሰኪያጅ እድማሱ በላይ፣ ህግ ወጥ ድርጊት የሞሳተፉትን ለይቶ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኖክ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ የሺዋስ ታደሰም እንዲሁ ችግሩን ለመፍታት በጋራ መስራት አስፋለጊ መሆኑ በህገ ወጥ መልኩ የሚንቀሳቀሱትን ማጋለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም