ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት የአፍሪካ አገራት አጀንዳ 2063ን ከማስፈጸም አንጻር በኢኮኖሚ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያከናወኑት ስራ የሚገመገምበት መድረክ ነው።

ዛሬም የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት 3ኛ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ እና 34ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

የአቻ መገማገሚያ ስርአት መድረኩ ያለፈውን አንድ አመት የስራ እንቅስቃሴ ሪፖርት አጽድቋል።


 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በመድረኩ የተለያዩ አገራት የአቻ ግምገማ ውጤት ማቅረባቸውን ጠቅሰው ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ የአገራት መሪዎች አቀባበላቸውን ማስቀመጣቸውን ጠቁመዋል።

በመድረኩ አፍሪካዊ የምዘና ስርአት ያለው ኤጀንሲ መቋቋሙን ገልጸው ይህም ትልቅ እመርታ መሆኑን አንስተዋል።

አፍሪካ ምን ያህል አዋጭ ናት ለሚለው የራስ ምዘና አለመኖሩ የአፍሪካን እውነታ ታሳቢ ያላደረጉ ሪፖርቶች እንዲወጡ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህም ኢንቨስትመንት እና ፋይናንስ ለመሳብ በሚደረገው ስራ ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ገልጸው ኤጀንሲው አፍሪካን የሚመስል ነጻ እና ብቁ ተቋም መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የሚያግዝ አህጉር በቀል ስርአት መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአት ከምስረታው አንስቶ ትልቅ ሚና ስትጫወት መቆየቷን ተናግረዋል።

አሁንም በተለያዩ መንገዶች ስርአቱን በማጠናከር ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአቻ ግምገማ ስርአትን ከመሰረቱ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።

መድረኩ የአፍሪካ አጀንዳ 2063 የልማት ግቦችን ተፈጻሚ ከማድረግ አኳያ ምን ተከናወነ? ምን አይነት ስራዎች ይቀራሉ? የሚለውን በስፋት የሚዳሰስበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም