ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በልማት የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ እንደምታሳካ ጠንካራ እምነት አለን- አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፤የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በልማት የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ እንደምታሳካ ጠንካራ እምነት አለን ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥ በውይይታቸው የድርጅቱና የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ትብብር ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በልማት እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ መገንዘባቸውን ጠቅሰው፥ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሎችን በማሳየት የከፍታ ጉዞዋን እንደምታሳካ ጠንካራ እምነት አለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ለቀጣናው ሰላምና ልማት እያበረከተች ያለውን ጉልህ ሚናም አድንቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር እና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የትብብር ጉዳዮች ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም