የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከቻይና መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከቻይና መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤የካቲት 7/2017 (ኢዜአ)፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መንግሥት የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ሊ ዩሺ ጋር ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ኢትዮጵያ እና ቻይና በሁኔታዎች የማይለወጥ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የመሠረቱ መሆኑን አስታውሰዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ የልማት ጥረቶች ቁልፍ አጋር መሆኗንም በውይይት ወቅት ገልጸዋል።
የውጭጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ለልዩ ተወካዩ በአፍሪካ ቀንድ እና አሕጉራዊ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
የቻይና የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ ተወካይ ሊ ዩሺ ልዩ ተወካዩ ሊ ዩሺ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ እንደሆነ ገልጸዋል።
በየጊዜው የሚደረጉ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የጉብኝት ልውውጦች የሁለቱን አገራት ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ልዩ ተወካዩ በቻይና አፍሪካ መድረክ(ፎካክ) የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ንግድ እና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ድጋፋችንን እናጠናክራለን ነው ያሉት።
ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 55ኛ ዓመት እያከበሩ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።