የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅትን የቱሪስት መዳረሻነቱን እንዲያጠናክር ጥረቶች እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅትን የቱሪስት መዳረሻነቱን እንዲያጠናክር ጥረቶች እየተደረጉ ነው

ድሬደዋ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅትን የቱሪስት መዳረሻነቱን እንዲያጠናክር ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።
የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅት የስራ እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሂዷል።
122 አመታት ያስቆጠረው የድሬደዋ የቀድሞ የባቡር ጣብያ ለድሬደዋ ከተማ ማበብ ትልቅ መሠረት መጣሉ ይታወቃል።
ምድር ባቡሩ በአሁኑ ወቅት ከድሬደዋ ደወሌ በሳምንት ሁለት ቀናት 208 ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ ለድሬደዋና ለሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ዘመን ተሻጋሪው የድሬደዋ ባቡር ጣቢያ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ቱሪስቶች መዳረሻነት ከማገልገሉ ባለፈ በቴክኒክና ሞያ ተቋማት የሚሰለጥኑ ወጣቶች ክህሎት መር የትብብር ስልጠና መስጠቱም በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
ውይይቱን የመሩት የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅት የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የከተማዋ ቅርስ የሆነው የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅት ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ አግዟል።
በሌላ በኩል የባቡር ጣቢያው የጥገና ክፍል የአስተዳደሩ ተሸከርካሪዎች በአነስተኛ ወጪ በመጠገን ብክነትን ለማስቀረት እንዳስቻለ ተናግረዋል።
እነዚህ አገልግሎቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ አስተዳደሩና ቦርዱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል።
የድሬደዋ ደወሌ ምድር ባቡር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አየለ ወልደ ዮሃንስ በበኩላቸው የድርጅቱን አገልግሎቶች የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የባቡር ጣብያውን ተርሚናል ቅርሱን በጠበቀ መንገድ በመጠገን ለስራ እና ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ጣቢያው የትራንስፖርት አገልግሎት ችግሮች ከማቃለል በተጨማሪ በከተማው ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲ ጋር በመቀናጀት ለ92 ወጣቶች ክህሎት መር ስልጠና በመስጠት ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል።