አምራች ኢንዱስትሪን በገጠር በማስፋፋት ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ይሰራል - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪን በገጠር በማስፋፋት ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ይሰራል - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት
አዳማ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፡- አምራች ኢንዱስትሪን በገጠር በማስፋፋት ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ።
የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ለሚዲያ አካላት የተዘጋጀ የስልጠና መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ(ዶ/ር) አምራች ኢንዱስትሪዎች በታላላቅና ዋና ዋና ከተሞች የታጠሩ በመሆኑ ይህንን መቀየር አስፈልጓል።
ዘርፉ ከሚያስገኘው ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታ አንጻር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መሠረቱ መስፋት እንዳለበት ገልጸው ከዚህ አንፃር የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን ስትራቴጂ ተቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
ወደ ሙሉ ትግበራ ከመገባቱ በፊት በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት እና ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህ መድረክም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል መስፋፋት ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ጥሬ እቃዎች ላይ እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል።
እንዲሁም አዳዲስ አሰራሮችና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወደ አምራች ዘርፉ እንዲገቡ በማድረግ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን መገንባት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን ከአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ጋር ተስማሚነት ባለው መልኩ የሚተገበር በመሆኑ በዚህ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን አካላት ሚና የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የስራ አመራር ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ከላሊ ወልደገብርኤል በበኩላቸው ተቋሙ አዳዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ለመፍጠር እና ያሉትን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በስልጠና፣ በማማከር፣ በገበያ ልማት፣ በፋይናንስ አቅርቦትና የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎች እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ይህም አምራች ዘርፉ በምርትና ምርታማነት፣ በስራ ፈጠራ፣ በተኪ ምርት ማምረትና በወጪ ንግድ ውጤታማ እንዲሆኑ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የከተማና የገጠር ኢንዱስትሪዎች ተቋማት የተሳሰረና የተመጋገበ እድገት እንዲኖራቸው ለማስቻል ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው ስልጠና ላይ ከገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ጋር በተያያዙ ሰነዶች ላይ ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።