ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስታወቁ።

ሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ የሚመክረው የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቦት ቢን ናህያን አልናህያን፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ጠንካራ ወዳጅነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያላቸው ጎረቤት አገሮች ናቸው።

ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ህዝብ ጎን ትቆማለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል።


 

በዚህም ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሚውል 15 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎችም ለሰላማዊ መፍትሄ እንዲሰለፉም ጥሪያቸው አቅርበዋል።

በተለይ መጪው የረመዳን ቅዱስ ወር በሱዳን ሰላም ለማስፈንና ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ መልካም እድል አድርጎ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ አሁን ላይ በሱዳን 30 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ ይህም ከአገሪቷ ጠቅላላ የህዝብ ብዛት 64 በመቶ ያህል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም