በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ሚሊዮን በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን ተሰጠ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ)፦በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ሚሊዮን 50 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን መሰጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።
የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የፌዴራልና የክልሎች የንግድ ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ዛሬ አካሂደናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ 6 ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ሚሊዮን 50 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በኦንላይን መሰጠቱን ገልጸዋል።
ከጠቅላላው ሀገራዊ የወጪ ንግድ 3 ነጥብ 28 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 1 ነጥብ 71 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።
የቅዳሜና እሁድ ግብይት ማዕከላትን 1 ሺህ 213 ማድረስ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
የሲሚንቶ ግብይት ላይ በተወሰደ የአሰራር ስርዓት ማሻሻያም የተረጋጋ አቅርቦትና ግብይት እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ዋጋው በግማሽ እንዲቀንስ መደረጉን ገልጸዋል።
በስድስት ወሩ ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ የጥራት መንደር ከ7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው በተቋሙ ቅጥር ግቢ 730 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከልም የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት አቅሞችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስርን በማጠናከር አስተማማኝ የገበያ እድል ከመፍጠር አንጻር የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡