የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የመዲናዋ ልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ናቸው- አካል ጉዳተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የመዲናዋ ልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ናቸው- አካል ጉዳተኞች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2017(ኢዜአ):- ባለፉት ዓመታት የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የልማት ሥራዎች በስፋት መከናወናቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች ገለፁ።
አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አካል ጉዳተኞች መካከል አቶ ከተማ ባይለየኝ፣ ወይዘሮ አለሚቱ ተፈራና አቶ አድባሩ ይገርማል ከዚህ በፊት በመዲናዋ መንገዶች በየጊዜው የሚደረጉ መቆፋፈሮች አስቸጋሪና ላልታሰበ አደጋ የሚዳርጉ ነበሩ።
በተለይም ዐይነ ስውራን ክፍት በተተው ጉድጓዶች እየወደቁ ሕይወት እስከማጣት የሚደርስ ተጨማሪ ጉዳት መዳረጋቸውን አንስተዋል።
በእግረኛ መንገዶች ላይ የሚከማቹ የግንባታ ተረፈ ምርቶችና የወደቁ ቁሳቁሶች የአካል ጉዳተኛን እንቅስቃሴ የሚገድቡ እንደነበሩ ገልጸዋል።
ዐይነ ስውራን በእግረኛ መንገድ ላይ ከሚተከሉ ዛፎች እና የመብራት ምሰሶዎች ጋር የመጋጨት ዕድላቸው ሰፊ እንደነበርም እንዲሁ።
የኮሪደር ልማቱ ግን ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ መገንባቱን ጠቅሰው፤ አመስግነዋል።
በእግረኛ መንገዶች የነበሩ የግንባታ ተረፈ ምርቶች መወገዳቸው እና ለዐይነ ስውራንና ለአካል ጉዳተኛ መንቀሳቀሻ ቢጫ ምልክቶች መገፋፋትን በማስቀረት በነጻነት እንዲጓዙ ማስቻሉን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዐይነ ስውራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ረታ ቀደም ባሉ ጊዜያት ጉድጓዶች፣ የመብራትና የስልክ ምሰሶዎች ተጨማሪ የአካል ጉዳት ያስከትሉባቸው እንደነበረ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የልማት ፕሮጀክቶች ምቹ አካባቢን በመፍጠር፣ በትምህርት ተደራሽነትና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።