ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ የጋራ ትርክቶችን በመሰነቅ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል

ቡታጅራ፤ የካቲት 6/2017 (ኢዜአ)--በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ የጋራ ትርክቶችን በመሰነቅ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ስለ ኢትዮጵያ" በሚል የተዘጋጀውና በሀገራዊ ሰላምና የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ ያተኮረው የውይይት መድረክ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ የጋራ ትርክቶችን በመሰነቅ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ለሦስት አስርት ዓመታት ሀገራዊ እሴቶች በማኮሰስ የተዛቡ ትርክቶች እንዲጎሎ በመደረጉ ብዙ ዋጋ ማስከፈሉን አስታውሰዋል።

ይህንን አስተሳሰብ በመቀየር ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር አሰባሳቢና የወል ትርክቶችን በማጎልበት ለጋራ ዓላማ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

ይህም ሀገራዊ እድገትን በማፋጠን ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች መካከል ገዥ ትርክትን ለማጎልበት እየተሰራ ያለው ሥራ አንድነትን በማጠናከር ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ እሳቤዎችን በማጠናከር ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለሰላም መጠናከር ሁሉም ቅንጅት መስራት እንዳለበት አስገነዝበዋል።


 

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት የሀገርን ሁለንተናዊ እሳቤዎችን ከግብ ለማድረስ ሰላምን ማጽናት የመጀመሪያው አማራጭ ነው፡፡ 

የኖሩ እሴቶቻችንን በማጠልሸት በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ውጥኖችን ለማሰናከል በተለያየ መንገድ የሚሰሩ አካላት ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል።

እነዚህን አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በማድረግ ዘላቂ ሰላምና አብሮነት የተረጋገጠባት ሀገርን ለመገንባት በጋራ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻልና ከተረጂነት ለመውጣት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለአብነትም ምርታማነትን በማሳደግ ከራስ ባለፈ ለውጪ ገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በዘርፉ የተገኘውን ስኬት አጠናክሮ በማስቀጠል ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ቀጣይነት ያለው ሰላም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።


 

"ሀገሪቱ ያሏትን ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በአግባቡ በማልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቂ ሀብት ያለን ህዝቦች ነን" ያሉት ደግሞ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሀየሶ ናቸው፡፡

በተለይም በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖን ጨምሮ በዓመት ከሦስት ጊዜ በላይ በማምረት ከእራስ ባለፈ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት ምቹ ስነ ምህዳር መኖሩንም አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው "ስለ ኢትዮጵያ" የተሰኘው የውይይት መድረክ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ የውይይት ባህልን በማጎልበት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር  የራሱን አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የገነቡ ሀገራት በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ያለፉና ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት የቻሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ወቅቱ አፈ ሙዝ የምንመርጥበት ሳይሆን የንግግርና የምክክር አብዮት አስፈላጊ በመሆኑ በጋራ መወያየትን ማጎልበት ይገባል ሲሉም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህብረተሰቡን ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋና እሴት በመጠቀም የወል ትርክትን ለመንገባት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም