ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ የረመዳን የፆም ወርን እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመልካም ተግባራት ማሳለፍ አለበት

 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፡- ህዝበ ሙስሊሙ የረመዳን የፆም ወርን እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመልካም ተግባራት ማሳለፍ እንደሚገባው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ዑላማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሃጂ ኢብራህም ቱፋ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሁለተኛ መደበኛ ዓመታዊ የኡለማዎች፣ የኢማሞችና የዱአቶች ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።

በኮንፈረንሱ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፤ ታላቁ የረመዳን ወር ፆም አቀባበል አስመልክቶ ትኩረት እንደሚደረግ ተገልጿል።

በኮንፍረንሱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ዑላማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የአዲስ አበባ ዑለማ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ፣ ኢማሞች፣ ኡለማዎችና ዱአቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ዑላማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሃጂ ኢብራህም ቱፋ፤ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ህዝብ ሙስሊሙ የረመዳን የፆም ወርን በመልካም ተግባራት ማሳለፍ ይኖርበታል ብለዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የዑለማ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ ባደረጉት ንግግርም በመንፈሳዊ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ዑላማዎች በመጪው የረመዳን የፆም ወር ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እውቀትን የሚያካፍሉበት መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

በሌላ መልኩ ለተቸገሩ ወገኖችና ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራትን ጨምሮ መልካም ተግባራትን እንዲከናወኑ እንደሁልጊዜው ሁሉ ማህበረሰቡን ማስተማር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም