የዋልያ ዝርያን ዘላቂ ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዋልያ ዝርያን ዘላቂ ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ እየተዘጋጀ ነው
ጎንደር፤ የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የዋልያ ዝርያ ዘላቂ ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የስትራቴጂክ እቅዱ ዓላማ በፓርኩ ክልል የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደንን በማስቀረት የብርቅዬው የዋልያ ዝርያን ዘላቂ ደህንነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡
ስትራቴጂክ እቅዱ እየተዘጋጀ የሚገኘው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የፍትህ፣ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
"ብሔራዊ የዋልያዎች ማገገሚያና መጠበቂያ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ስትራቴጂክ እቅዱ መድረኮችን በማዘጋጀት እቅዱን ማዳበር የሚያስችሉ ግብአቶችን የማሰባሰብ ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ህገ-ወጥ አደንን በመቆጣጠርና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የዋልያዎችን የመኖሪያ አካባቢ ከአደጋ ስጋት ነጻ በማድረግ ቁጥራቸውን በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የዋልያዎችን የጤናና የውልደት ምጣኔ ለማሻሻል የሚያግዙ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ማካሄድና የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
እቅዱን ዘንድሮ በማጠናቀቅ በቀጣዩ ዓመት በብሔራዊ ደረጃ በሚመለከተው አካል በማጸደቅ ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ጠቁመዋል።
እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍን መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በፓርኩ ውስጥም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡