የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ ነው

አሶሳ፤የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፦የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በአሶሳ ከተማ አስተዳደር እና በክልሉ መንግስት ወጪ የ10 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ ውስጥ በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወነ የሚገኘው የ4 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማቱ ከተጀመረ አንድ ወር ሆኖታል።

የኮሪደር ልማቱ በተለምዶ አዲሱ አስፓልት በሚባለው አካባቢ ግራና ቀኝ እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የፍሳሽ ማስወገጃ እና የመሬት ላይ ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው።

በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት አቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አጠይብ አወድ እንደገለፁት፥ የኮሪደር ልማቱን ለአራት ተቋራጮች በማከፋፈል ስራው በፍጥነት እንዲከናወን እየተደረገ ነው።

የኮሪደር ልማቱን የሚከታተል ቡድን በማቋቋም ስራው በጥራት እንዲሰራም ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን የተናገሩት ሰብሳቢው፤አሁን ካለው የስራው ፍጥነት አንፃር ቀድሞ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማቱ የመዝናኛ፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ ፋውንቴን፣ ፓርኪንግ፣ መፀዳጃ ቤት እና ሌሎችንም ያካተተ እንደሆነ ገልፀዋል።

የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት እና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ያደርጋታል ሲሉም አክለዋል።

የአሶሳ ከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ይማም ይመር በበኩላቸው፥ አስፈላጊውን የሰው ሃይል እና ማሽነሪዎችን በመጠቀም ስራው በፍጥነት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች የመሬቱ አቀማመጥ ተዳፋት በመሆኑ ተጨማሪ የግንባታ ስራ እንድናከናውን አድርጎናል ያሉት መሃንዲሱ ከዚህ በኋላ የማንጠፍ ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ በፍጥነት እንዲከናወን አመራሩ በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ ተቆጣጣሪ መሃንዲሱ ገልፀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከሚያከናውነው የኮሪደር ልማት በተጨማሪ ከአሶሳ ከተማ የአስፓልት ስራ ጋር የተያያዘ የ5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ግንባታ በክልሉ መንግስት እየተከናወነ መሆኑም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም