በትምህርት ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አቅም ፈጥረዋል - የትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ዘርፍ የተደረጉ ማሻሻያዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አቅም ፈጥረዋል - የትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2017(ኢዜአ)፡- መንግስት በትምህርት ዘርፍ ያደረጋቸው የአሰራር ማሻሻያዎች ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ አቅም መፍጠራቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ መንግስት በትምህርት ዘርፍ ላይ ያከናወናቸውን ዐበይት ተግባራት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት መስኩ ላይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን በዚሁ ወቅት አስረድተዋል፡፡
በለውጡ ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አመርቂ ለውጥ ማስመዝገብ የሚያስችሉ የአሰራር ስርአቶች ተዘርግተው ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደታቸውን ከአካባቢያቸው ጸጋ ጋር በማቀናጀት እንዲያስኬዱ አሰራር ተዘርግቶ ስራ ላይ መዋሉንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ተቋማቱ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚያስችላቸውን የራስ ገዝ ስርአት በመዘርጋት ወደ ስራ መገባቱን አክለዋል።
በመማር ማስተማር ሂደት ይታዩ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ማነቆዎችን ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ልዩ ልዩ የሪፎርም እና የአሰራር ማሻሻያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።
ፓርቲው በንድፈ ሀሳብ ላይ የተመሰረተውን ስርአተ ትምህርት ከክህሎት ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ ማድረጉን አብራርተዋል።
መንግስት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ትውልድን በእውቀትና በክህሎት ለማነጽ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ማህበረሰቡን ያሳተፈ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስታውቀዋል።
በዚህም 39 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ከደረጃ በታች የነበሩ የትምህርት ተቋማትን የማደስ እና አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋት ስራ መከናወኑን አክለዋል።
በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር በትምህርት ዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን አብራርተዋል።